ወደ ዋና ይዘት ይሂዱ
ስንክሳር

Appearance

ቀን መቁጠሪያ

ብሔራዊ በዓላት

ፋሲካ (ትንሣኤ)

ትንሣኤ ማለት ተንሥአ ካለው የግዕዝ ግሥ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም መነሣት ወይም አነሣሥ ማለት ነው። እስራኤል ዘሥጋ ያከብሩት የነበረው በዓለ ፋሲካ ከባርነት ቀንበር ወደ ነፃነት የተላለፉበት፣ ከኀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገረበት በዓል ነበር። የሐዲስ ኪዳን በዓለ ትንሣኤ ግን እስራኤል ዘነፍስ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የተመለስንበት፣ ከሐሳር ወደ ክብር፣ ከአሮጌው ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው። ፋሲካ ከዕብራይስጥ «ፔሳሕ» ማለት ሲሆን ትርጉሙም ማዕዶት ወይም መሸጋገሪያ ማለት ነው። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና እምነት መሠረትና የምእመናን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማረጋገጫ ነው። መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በተጻፈው መሠረት የመስቀልን ፀዋትወ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ፣ ሙታንን በሞቱ ሕያዋን ያደርጋቸው ዘንድ በዕለተ ዓርብ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። በዕለተ ዓርብ የፈጠረውን አዳም በፈጸመው በደል ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ነፃ ይሆን ዘንድ፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት አምላክ በመስቀል ላይ ዋለ። ወዳጆቹ አርማትያሱ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሥጋውን አውርደው በጥሩ ሐር በተሠራ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት። አይሁድም “በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ብሏልና ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው እንዳያስቱ” በሚል ሐሳብ መቃብሩን በጭፍሮች አስጠብቀው በማኅተም አትመውት ነበር። ጌታችን በከርሠ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው። በሦስተኛው ቀን በሌሊተ እሑድ ኃጢአትን፣ ሞትንና መቃብርን ደምስሶ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተነሥቷል።

ዐቢይ ጾም (ሁዳዴ ጾም) እና ሰሙነ ሕማማት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ ከተጠመቀ በኋላ ዐርባ ቀን የጾመው፣ 55 ቀናት የሚፈጀውን ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ) የትንሣኤ በዓል ከመድረሱ በፊት ይጾማል። በውስጡ ስምንት ቅዳሜዎች፣ ሰባት እሑዶች ይገኛሉ፡፡ ይኸውም ዐሥራ አምስት ቀን ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቀናት ከጥሉላት እንጂ ከእህል ውኃ ስለማይጦሙ የጦሙ ወራት ዐርባ ቀን ብቻ ይሆናል። በስምንት ሳምታት ተከፋፍሎ ሳምንታቱ የየየራሳቸውን ስያሜ ይዘው ይታሰባሉ። የመጨረሻው የጾሙ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል።

የቅዱሳት አንስት ምስክርነትና የሐዋርያት መገለጥ

ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ የሄዱት ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም ባወፍልያና እና ሰሎሜ ቀዳሚ የዓይን ምስክሮች ነበሩ። መልአኩም «የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ከዚህ የለም፣ ተነሥቷል» የሚለውን የምሥራች አበሠራቸው። ሴቶቹም በደስታ ተሞልተው ዜናውን ለሐዋርያት ሲያደርሱ ጌታችን በመንገድ ተገለጠላቸው። ሐዋርያትም ጌታን ገጽ በገጽ አይተው ሰግደውለታል።

ዳግም ትንሣኤ (የቶማስ ሰንበት)

የሰሙነ ትንሣኤ መጨረሻው ስምንተኛው ቀን ዳግም ትንሣኤ ይባላል። ዳግም ትንሣኤ የተባለበት ምክንያት የሐዋርያው ቶማስ ምስክርነት የሚታሰብበት ዕለት ነው። ጌታችን በዝግ ቤት ውስጥ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ «ጣትህን ወደዚህ አምጣ፣ እጆቼንም እይ፤ እመን እንጅ ተጠራጣሪ አትሁን» ሲል ቶማስም «ጌታዬ አምላኬ ሆይ» ብሎ መስክሮበታል።

የትንሣኤ አከባበር

ትንሣኤ በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ሁልጊዜም የሚውለው እሑድ ቀን ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትንሣኤ በዓል አከባበር የሚደረገው በዕለተ ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ በሚደረግ ማኅሌትና ቅዳሴ ነው። ምእመናን ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይጎርፋሉ። «ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሰሮ ለሰይጣን፤ አግዐዞ ለአዳም፤ ሠላም እምይዕዜሰ፤ ኮነ፤ ፍስሐ ወሠላም፡፡» (“ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ሠላም ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ሆነ”) እየተባለ በቅዳሴው ላይ ይታወጃል። ከትንሣኤው ቀን በኋላ ለሚቀጥሉት 50 ቀና የደስታ ቀናት ሆነው እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ድረስ ትንሣኤው ይከበራል።

የዕለቱን ቀን እና የቀን መቁጠሪያ ዝርዝር በመተግበሪያው ይመልከቱ።

ቀን መቁጠሪያውን በመተግበሪያው ይክፈቱEnglish