ወደ ዋና ይዘት ይሂዱ
ስንክሳር

Appearance

ቀን መቁጠሪያ

ብሔራዊ በዓላት

ጥምቀት

በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው ጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ቀኖና መሰረት ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው። የሚከበረውም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ30 አመቱ የማዳን ሥራውን በጥምቀት የጀመረበትን ጊዜ ለማስታወስ ነው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቋል፤ ያጠመቀውም መጥምቁ ዮሐንስ ነው። ይህ በዓል በግሪክ ቋንቋ ኤጲፋንያ ይባላል ትርጓሜውም «መገለጥ» ወይም «አስተርእዮ» ማለት ነው። በዚህ ዕለት መለኮት ልዩ የሆነች የሦስትነቱን ምሥጢር ገልጦባታልና፤ አብ ከሰማይ ሆኖ “የምወደው በርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” እያለ ሲመሰክር ወልድም በዮርዳኖስ ወንዝ ቁሞ ሳለ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል በወልድ ራስ ላይ ተቀምጧል። ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ እንደተጠመቀ ለማስታወስ በየዓመቱ ጥር 10 ቀን ሁሉም ታቦታት በዋዜማው ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው በአደባባይ በሊቃውንቱ እና በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም በምእመናን በዝማሬ ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመውረድ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ ዳር ወይም በሰው ሠራሽ የውሃ ግድብ አጠገብ በዳስ ወይም በድንኳን ያድራሉ። ይህም ዕለት “ከተራ” ይባላል፡፡ ከተራ የሚለው ቃል «ከተረ» ሰበሰበ፣ከበበ፣ ያዘ፣ ገደበ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ይህ ዕለት ከተራ የተባለው በአካባቢው ያለው ውኃ እንዳይፈስ ተገድቦ ሕዝቡ እንዲጠመቅበት ስለሚዘጋጅ ነው፡፡ ሌሊቱንም በማኅሌትና በቅዳሴ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ሥርዓተ ቅዳሴው ይፈጸማል። ሲነጋም በወንዙ (በተከተረው ውሃ) ዳር ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል። ወደ ከተራው የወረዱት ታቦታት ከሚካኤል ታቦት በስተቀር በአደባባይ ታጅበው ወደመንበራቸው ይመለሳሉ።

ቃና ዘገሊላ

በጥምቀት በዓል ማግስት ጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል። በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ክፍል ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና በዶኪማስ ቤተ በተደረገ ሠርግ ከእናቱ ከድንግል ማርያም እንዲሁም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኝቷል። በሠርጉ ቤትም ሥርዓቱ እየተከናወነ ሳለ የተዘጋጀው የወይን ጠጅ አለቀባቸው። ይህን የተገነዘቡት ዶኪማስና አስተናባሪዎቹ ተደናግጠው ሳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የወይን ጠጁ ማለቁን ተረድታ ጭንቀታቸውን ወደሚያቀልለው ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ዘንድ ቀርባ “ልጄ የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው። እርሱም መልሶ “አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። በቦታው የነበሩትን ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዘቻቸው፡፡ እያንዳንዱም ጋን ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር፡፡ አስተናባሪዎቹም ውኃውን በጋኖቹ ሞልተው አቀረቡለት፣ ውኃውንም ወደ ወይን ለወጠው፡፡ እነርሱም እየቀዱ ለታዳሚዎች አቀረቡ፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው በሌላ ጊዜ ቢሆንም የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ጥር 12 ይከበራል። ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር በማሰብ ነው። በዚህ ዕለትም የቅዱስ ሚካኤል ታቦት ወደ መንበሩ በአደባባይ ታጅቦ ይመለሳል።

የዕለቱን ቀን እና የቀን መቁጠሪያ ዝርዝር በመተግበሪያው ይመልከቱ።

ቀን መቁጠሪያውን በመተግበሪያው ይክፈቱEnglish