ወደ ዋና ይዘት ይሂዱ
ስንክሳር

Appearance

ቀን መቁጠሪያ

ብሔራዊ በዓላት

ስቅለት

ዕለተ ዓርብ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የሚታሰብበት ቀን ነው። «ስቅለት» የሚለው ቃል «ሰቀለ» ከሚለው የግሥ መሠረት የተገኘ ሲሆን፣ ወንጀለኞች በመስቀል እንጨት ላይ ተሰቅለው የሚቀጡበትን መከራና ስቃይ ያመለክታል። ጌታችን ግን አንዳች ኃጢአት ሳይሠራ፣ ስለ ሰው ፍጡር ፍቅር ሲል ያለምንም በደል ራሱን ለቤዛነት አሳልፎ የሰጠበት ቅዱስ ዕለት ነው። ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ። ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት። አይሁድ ምንም ዓይነት ጥፋት ሳያገኙበት ለሞት አሳልፎ እንዲሰጥ በግድ ጠየቁ። ጲላጦስም «እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም» ቢልም፣ ዓለምን ያድን ዘንድ ፈቃዱ እንዲፈጸም አደረገ። ጌታችን እጅግ ከባድ ውርደትን፣ ግርፊያን፣ የእሾህ አክሊልና መስቀል ተሸክሞ ወደ ጎልጎታ ተራራ ሄደ። በዚያም ከሁለት ወንበዴዎች መካከል ተሰቅሎ ነፍሱን ሰጠ።

የ13ቱ ሕማማተ መስቀል (በመስቀል የተቀበላቸው መከራዎች)

ጌታችን ስለ እኛ ሲል የተቀበላቸው 13ቱ ሕማማተ መስቀል የሚከተሉት ናቸው፡

  • ራሱን በዘንግ ተመታ
  • በጥፊ ተመታ
  • ምራቅ ተፉበት
  • የሾኽ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ አቀዳጁት፤ በአዳም ኃጢአት ምክንያት «ምድር እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች» ተብሎ የተነገረውን ርግማን ለመደምሰስ ራሱ በእሾህ ቆስሏል።
  • መራራ ሐሞት አጠጡት፤ መራራውን ሐሞት በመቅመሱ ከእኛ ላይ መራራው ሞት ጠፍቷል።
  • ጀርባውን መገረፍ
  • ጎኑን በጦር ተወጋ፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ወጣ
  • ወደ ኋላ መታሰሩ
  • 5ቱ ቅንዋተ መስቀል (ችንክሮች)፦
  • ሳዶር ፦ ቀኝ እጁ የተቸነከረበት
  • አላዶር ፦ ግራ እጁ የተቸነከረበት
  • ዳናት ፦ እግሮቹ የተቸነከረበት
  • አዴራ ፦ ደረቱን የተቸነከረበት
  • ሮዳስ ፦ ከወገቡ (እብረቱ) አጣብቆ እንዲይዝ የተቸነከረበት ናቸው። (እነዚህም በሰው ልጆች ላይ ለ5,500 ዘመን የሠለጠነውን የሞት ችንካር ሰባብረዋል)።

በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸው 7ቱ የፍቅር ቃላት

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ታላላቅ ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፦

  • «ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?)»
  • «እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ»
  • «አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ»
  • «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው»
  • እመቤታችንን «ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ»፤ ደቀ መዝሙሩንም «እናትህ እነኋት» በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት አከናወነ
  • «ተጠማሁ»
  • «ሁሉ ተፈጸመ»

በስቅለት ዕለት የተፈጸሙ 7ቱ ታላላቅ ተአምራት

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ሰማይና ምድር ፈጣሪያቸውን በማስባቸዉ የሚከተሉት ሰባት ታላላቅ ተአምራት ተደርገዋል፦

  • ፀሐይ ጨለመች
  • ጨረቃ ደም ለበሰች
  • ከዋክብት ብርሃናቸውን ነሡ
  • የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከሁለት ተከፈለ፤
  • አለቶች ተሰነጣጠቁ
  • መቃብራት ተከፈቱ
  • የሞቱት (ሙታን) ተነሡ

የዕለተ ዓርብ ሥርዓት

በዕለተ ዓርብ ከጠዋት ሦስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዐሥራ አንድ ሰዓት ድረስ በልዩ ልዩ ሥርዓት እና በስግደት ይከበራል። በስቅለት ሥርዓተ አምልኮ ጊዜ በብዛት የሚነገረው «ኪርያላይሶን» የግሪክ (ጽርዕ) ቃል ሲሆን፣ አጠራሩም «ኪርዬ ኤሌይሶን» ነው።

  • ኪርዬ (Kirye): ጌታ ሆይ / አቤቱ ማለት ነው።
  • ኤሌይሶን (Eleison): ማረን / ይቅር በለን ማለት ነው።

በተለምዶ ሲጠራ ከ«ኪርዬ» እና ከ«ኤሌይሶን» ቃላት መካከል ያለው ጽንፍ ተቀራርቦ በአማርኛ አጠራር «ኪርያላይሶን» ተብሎ ይለመዳል። በሕማማት ሰዓታት ውስጥ «ኪርያላይሶን» በተለያዩ ዜማዎችና በናይናን (ለምሳሌ፦ ኪርያላይሶን አብናዲ ናይናን ኪርያላይሶን፣ ኪርያላይሶን ታኦስ ናይናን ኪርያላይሶን፣ ኪርያላይሶን ማስያስ ናይናን... እያሉ) እየተቀባበሉ ይሰገዳል።

እየሰገድን በቃል የምንቀበላቸው ተሰጥዖዎች፡

  • ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወዕዘዝ እስከ ለዓለም (ለአንተ ኃይል ክብር ጌትነት ገዥነት ለዘለዓለሙ ገንዘብህ ነው)
  • አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወዕዘዝ እስከ ዓለም (ፈጣሬዬ አማኑኤል ሆይ ኃይል ክብር ጌትነት ገዥነት ለዘለዓለሙ የአንተ ነው)
  • ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወዕዘዝ እስከ ለዓለም (ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ኃይል ክብር ጌትነት ገዥነት ለአንተ ይገባል)
  • ኃይልየ ወፀወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ... (ኃይሌና አምባዬ መጠጊያዬ እርሱ ጌታዬ ነው ረዳቴ ሆነህልኛልና...)

ጠዋት ሦስት ሰዓት፡

  • መዝሙር፡ «እግዚኦ ኢትጸመመኒ ለክስትየ...» (መዝ. ፳፩፥፲፯) - አቤቱ ልመናዬን ቸል አትበል...
  • ንባባት: የማቴ. ፳፯፥፲፭-፳፮፤ የማር. ፲፭፥፮-፲፭፤ የሉቃ. ፳፫፥፲፫-፳፭፤ የዮሐ. ፲፱፥፩-፲፮ ተነበቡ።
  • ሕብረት/ሰገደት: «ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት አኃዝዎ ለኢየሱስ ወወስድዎ ይሰቅልዎ» (ሦስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ኢየሱስን ይዘው ይሰቅሉት ዘንድ ወሰዱት) እያሉ በሰገደት ይከበራል።

በስድስት ሰዓት (ቀትር):

  • መዝሙር፡ «ቀነዉኒ እደውየ ወእገርየ...» (መዝ. ፳፩፥፲፮-፲፯) - እጄንና እግሬን ቸነከሩኝ...
  • ንባባት: የማቴ. ፳፯፥፳፯-፵፭፤ የማር. ፲፭፥፲፮-፴፫፤ የሉቃ. ፳፫፥፳፯-፵፬፤ የዮሐ. ፲፱፥፲፫-፳፯።
  • ሕብረት/ሰግደት: «ጊዜ ስድስቱ ሰዓት ቀትር ሶቤሃ ሊቃነ ካህናት ሰቀልዎ ለኢየሱስ በቀራንዮ መካን» (ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ... የካህናት አለቆች ኢየሱስን ቀራንዮ ሰቀሉት) እየተባለ ይሰገዳል። ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ጨለማ ሆኖ ከቆየ በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ማታ እንደተለመደው ብርሃን ሆኗል («ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ» - ዘካ. ፲ፄ፥፯)።

በዘጠኝ ሰዓት:

  • መዝሙር፡ «ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ ወአስተዩኒ ብሒኣ ለጽምትየ...» (መዝ. ፷፰፥፳፩) - በምግቤ ውስጥ ሐሞት ጨመሩ...
  • ንባባት: የማቴ. ፳፯፥፵፮-፶፤ የማር. ፲፭፥፴፬-፴፶፤ የሉቃ. ፳፫፥፵፭-፵፮፤ የዮሐ. ፲፱፥፳፰-፴።
  • ሕብረት/ሰገደት: «ጊዜ ተሠዓቱ ሰዓት ጸርሓ ኢየሱስ በቃሉ ወይቤ ኤሎሄ ኤሎሄ...» (ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ ኢየሱስ ቃሉን አሰምቶ ኤሎሄ ኤሎሄ አለ)። ጌታችን «ተጠማሁ» ብሎ በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃና ትኩስ ደም አፈሰሰ (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)።

አሥራ አንድ ሰዓት (ማታ መግቢያ):

  • መዝሙር፡ «አንሣእኩ እደውየ ኀቤከ ነፍስየ ከመ ምድረ በድው ጸምዓተከ...» (መዝ. C፵፮፥፮)
  • ንባባት: የማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፮፤ የማር. ፲፭፥፴፰-፵፩፤ የሉቃ. ፳፫፥፵፯-፵፱፤ የዮሐ. ፲፱፥፴፩-፴፯።
  • ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬)። ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)። በዚህ ጊዜ በረሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገልጦ «ንሴብሖ ለእግዚአብሔር» እየተባለ ይዘመራል።

የዕለቱን ቀን እና የቀን መቁጠሪያ ዝርዝር በመተግበሪያው ይመልከቱ።

ቀን መቁጠሪያውን በመተግበሪያው ይክፈቱEnglish