ወደ ዋና ይዘት ይሂዱ
ስንክሳር

Appearance

ቀን መቁጠሪያ

ብሔራዊ በዓላት

መስቀል

መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እውነተኛው መስቀል በንግሥት እሌኒ መገኘቱን በማስታወስ በየዓመቱ መስከረም 17 (የደመራ በዓል ደግሞ መስከረም 16) በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ነው መስቀል "ሰቀለ" ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መስቀያ ወይም መከራ ማለት ነው። መከራም የተባለበት የጥንት ሮማውያን ወንጀለኛን በሞት የሚቀጡት በመስቀልያ እንጨት ላይ እየሰቀሉ ስለነበር ነው። አይሁድም ከገዥዎቻቸው በወረሱት ልማድ መሠረት ያለምንም ሀጥያት እና በደል አጥፊ ነው ብለው የፈረዱበትን ኢየሱስ ክርስቶስን ከወንበዴዎች ጋር በዕፀ መስቀል ሰቅለው በሞት ቀጡት።

የመስቀሉ መቀበር እና መልሶ መገኘት

ይህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል። በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑና ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ። የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ። ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር። በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተቀብሮ ኖረ። ከዚህ በኋላ የንግስት እሌኒ ልጅ ቆስጠንጢኖስ በ4ኛው መቶ ዓመተ ምህረት ገደማ በቁስጥንጥንያ እነደነገሠ፣ አብያተክርስትያናትን እያወደሙ አብያተ ጣዖታትን የሚያስፋፉ መክሰምያኖስ እና ድዮቅልጥያኖስ የሚባሉ አላውያን ነገሥታት ተነሥተው ክርስትያኖችን ያሰቃዩ ነበር። የነመክስምያኖስ ሥቃይ ያንገፈገፋቸው ክርስትያኖችም ከሥቃይና ከመከራ እንዲያድናቸው ቆስጠንጢያኖስን ዘወትር ይማጠኑት ስለነበር ምንም እንኳ ቆስጠንጢኖስ በዚያን ጊዜ የክርስትያን እምነት ተከታይ ባይሆንም የክርስትያኖች እልቂት መንፈሱን ስለነካው እነርሱን ለመርዳት ወሰነ። እሱም ራሱ በዘውዱ ላይ የመስቀል ምልክት ካሠራበት በኃላ ሠራዊቱ ሁሉ በፈረስ፣ እቃው፣ በጋሻው በጦርና በጎራዴው ላይ የመስቀል ምልክት እያደረገ እንዲከተለው አዘዘና ወደሮም ዘምቶ ያን የክርስቲያን ባላንጣ መክስምያኖስን ድል መትቶ ለቤተክርስትያን እና ለምእመናን ሰላምን መሥርቶ ተመለሰ፡፡ መንፈሱም ወደ ክርስትና ኃይማኖት ያዘነበለ ስለነበር አምኖ ተጠመቀ፡፡ ያን ያዩ የሮማን ምእመናን መስቀል የስጋና የነብስ መድሀኒታችን ነው በማለት ድል አድረጊው ቆስጠንንጢኖስን ትምህርተ መስቀል እየያዙ ተቀበሉት። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መስቀል የክርስትያን ምልክት፣ የድል አርማ መሆኑ ስለታወቀ በክርስቶስ ክርስትያን የተባለ ሁሉ በትምህርተ መስቀል ከማመኑም በላይ ማንኛውንም በመስቀል አምሳል እየቀረጸ በአንገቱ ማንጠልጠል፣ በእጅ መያዝ ጀመረ፡፡ ከዚህም በቀር ስለ መስቀል ፍቅር ያደረበት ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ ሰውነቱን በእሾህ እና በመርፌ እየወቀረ ትምህርተ መስቀል ያበጅ ጀመር፡፡ እሌኒ ንግስትም ልጅዋ ወደ ክርስትና ሃይማኖት የገባላት እንደሆነ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ አብያተ ክርስትያናትን ለማሳነጽ እና የተቀበረውንም መስቀል ለመፈለግ ብጽአት ነበራት። በአላውያኑ ነገስታት አርባ ዘመን ተዘግተው የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት ካስከፈተች በኋላ የተቀበረውን መስቀል ፍለጋ ጀመረች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቀድ ነበርና አንድ የአይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው፡፡ ሽማግሌውም “አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ እጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። እንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡ ይህ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪርያኮስ ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ.ም. ነበር፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶን እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ፡፡ ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት፡፡ በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ወይም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ለመሰቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ ተመርቆ የገባው (ቅዳሴ ቤቱ) የተከበረው መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም. ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረው መስከረም 17 በመሆኑ ነው፡፡

ዘመነ መስቀል

የመስቀል በዓል እና በዋዜማው የሚከበረው የደመራ በዓል በአንድነት ይከበራሉ። ደመራ ማለት መጨመር፣መሰብሰብ፣መከመር ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን ያስተባበረ መሆኑን ገልጸው የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የመስቀል በዓል በዋዜማውና በበዓሉ ቀን ብቻ አይወሰንም። መስከረም 10 ቀን ተቀጸል ጽጌ በሚል፣ መስከረም 16 ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓት፣ መስከረም 17 ቀን በጢሱ አመልካችነት ቁፋሮው የተጀመረበትና በጎልጎታ ቤተ ክርስቲያኑ ታንጾ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት፣ መስከረም 21 ቀን ቅዱስ መስቀሉ በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በግሸን ደብረ ከርቤ ያረፈበት ቀን እና ከመስከረም 17 ቀን እስከ መስከረም 25 ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት በቅዱስ ያሬድ የዝማሬ ሥርዓት መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ዘመነ መስቀል በመባል ይከበራል፡፡

ባህልና አከባበር

አዲስ አበባ

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የመስቀል ደመራበዓል ከኢትዮጵያ ትልልቅ ሕዝባዊ ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች አንዱ ነው። በመስቀል አደባባይ ትልቅ ደመራ ይገነባል፤ ከከተማዋ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚመጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መዘምራንና ካህናት በመስቀል ዝማሬ፣ በመዝሙርና በሥርዓታዊ ሰልፍ ያቀርባሉ። በዚህ ልዩ ሥነ ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በተገኙበት ደመራው ይለኮሳል፤ በዚያም አፍታ አደባባዩን የሚሞላው የሕዝብ ብዛት፣ የመዝሙሩ ድምፅና የሚለኮሰው የጧፍ ብርሃን በዓሉን የማይረሳ ሕዝባዊ ትዕይንት ያደርጉታል። በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚመጡ ምዕመናንና ጎብኚዎች፣ ከውጭ አገር የሚመጡ ቱሪስቶችም ይሳተፋሉ። የመስቀል አደባባይ ክብረ በዓል የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና እምነት በግልጽ ከማሳየቱም በላይ፣ የኢትዮጵያን ሕያው ባህላዊ ቅርስ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ታላቅ ዝግጅት ነው። ይህ በዓል በ2013 እ.ኤ.አ. በUNESCO የሰው ልጅ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቧል

ደቡብ ኢትዮጵያ

በደቡብ ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ትርጉሙ ባሻገር ጠንካራ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴት ያለው ክብረ በዓል ነው። በጉራጌ፣ በከምባታና በሌሎች የክልሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ በዓሉ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ የሚገናኙበት፣ የተለያዩ ማኅበራዊ ግንኙነቶች የሚጠናከሩበትና የጋራ ማንነት የሚገለጽበት ልዩ ወቅት ነው። በተለይ በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ለመስቀል የሚደረገው ዝግጅት ከበዓሉ ቀን በላይ የሚዘልቅ ሲሆን፣ በዓሉ ለዓመቱ የሚጠበቅ ባህላዊ ክስተት ነው። ቤተሰቦች ከተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ ከዘመዶቻቸው ጋር ይቆያሉ፤ ይህም በዓሉን የመሰባሰብና የመተሳሰብ ወቅት ያደርገዋል። በጉራጌ ባህል የመስቀል በዓል ከባህላዊ ጋብቻ ጋርም ጥብቅ ትስስር አለው። በእንቁጣጣሽና በመስቀል መካከል ባሉት ቅዳሜና እሁዶች ብዙ ወጣቶችና ቤተሰቦች ወደ ሀገር ቤት በመመለስ የሰርግ ሥነ ሥርዓቶችን ያከብራሉ። ስለዚህ መስቀል ለሰርግ ድምቀት ይጨምራል፤ ሰርጎችም የበዓሉን ደስታና ማኅበራዊ ድባብ ያበለጽጋሉ። በዓሉ የይቅርታ፣ የእርቅ፣ የመጋራትና የአንድነት መግለጫ በመሆኑም ትርጉሙ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ብቻ አይወሰንም። በደቡብ ኢትዮጵያ ያለው የመስቀልና ከእሱ ጋር የተያያዙ የአካባቢ ክብረ በዓላት ትስስር፣ ባህላዊ ልማዶች በማኅበረሰብ ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደሚቀጥሉና ከአካባቢያዊ ማንነት ጋር እንደሚዋሃዱ የሚያሳይ ምሳሌ ነው።

አጋሜ

በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምስራቅ (አጋሜ) በተለይም በአዲግራት ከተማ እና አካባቢው፣ የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ክብሩ ባሻገር ጥልቅ ማኅበራዊ ትርጉም ያለው ባህላዊ ክስተት ነው። በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ቤተሰቦች ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ ይገናኛሉ። በአጋሜ የሚታወቀው ጥሕሎ የተሰኘው ባህላዊ የጋራ ምግብ ከእነዚህ ልዩ ልማዶች አንዱ ነው፤ በዚህ ሥነ ሥርዓት ሰዎች በጋራ ተቀምጠው ምግብ ይካፈላሉ። በዓሉ በተጨማሪም በተጣሉ ሰዎች መካከል እርቅ እንዲፈጠር፣ የቤተሰብ ትስስር እንዲጠናከርና ማኅበረሰቡ በአንድነት እንዲሰበሰብ የሚያበረታታ ወቅት ነው። በአዲግራት ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በቀንዳዕሮ ተራራ ላይ የ22 ሜትር ከፍታ ያለው ግዙፍ መስቀል ተተክሎ የሚገኝ ሲሆን፣ የበዓሉ ማድመቂያና የከተማዋ መለያ ምልክት ነው።

የዕለቱን ቀን እና የቀን መቁጠሪያ ዝርዝር በመተግበሪያው ይመልከቱ።

ቀን መቁጠሪያውን በመተግበሪያው ይክፈቱEnglish