ወደ ዋና ይዘት ይሂዱ
ስንክሳር

Appearance

ቀን መቁጠሪያ

ብሔራዊ በዓላት

ገና (ልደቱ ለእግዚእነ)

ገና የሚለው ቃል ከጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ የተወረሰ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ልደት ማለት ነው። ታሕሳስ 29 ወይም በአራት ዓመት አንዴ ደግሞ (በዘመነ ዮሐንስ) ታህሳስ 28 ይከበራል። ገና ወይም ልደት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት ዐበይት የጌታችን በዓላት አንዱ ሲሆን፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው ሆኖ መወለድ የሚዘክር በዓል ነው። ይህም የቃል ሥጋ መሆንን፣ ማለትም የእግዚአብሔር ወልድ ለሰው ልጆች ድኅነት ሰው ሆኖ ወደ ዓለም መምጣቱን የሚያስታውስ በዓል ነው። የገና በዓል በዚህ መሠረት የክርስቶስን ልደት ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጆች ድኅነት በክርስቶስ የተገለጠበትን ታላቅ ምሥጢር የሚያስታውስ መንፈሳዊ በዓል ነው። የጌታችን ልደት በወንጌላት እንደተገለጸው፣ በቤተ ልሔም በትሕትና የተፈጸመ ታላቅ ምሥጢር ነው። ክርስቶስ በበረት መወለዱ፣ እረኞች የምሥራቹን መስማታቸውና ከመላእክትም ጋር «በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር፣ በምድርም ሰላም» ብለው ማመስገናቸው፣ የጥበብ ሰዎች እጅ መንሻ ይዘው መምጣታቸው ይዘከራል።

ጾመ ነቢያት

የገና በዓል ከመድረሱ ከአንድ ወር ከግማሽ በፊት “ጾመ ነቢያት” ወይም የገና ጾም ይጀምራል። ነቢያት የጌታን መምጣት በትንቢት የገለጹበትንና ለእርሱም መምጣት በተስፋ የጠበቁበትን ዘመን የሚያስታውስ ሲሆን፣ ምእመናንም የጌታችንን ልደት በመንፈሳዊ ዝግጅት እንዲቀበሉ ያደርጋል።

ባህልና አከባበር

ከገና በዓል ጋር በተለይ የሚያያዘው ባህላዊ ጨዋታ የገና ጨዋታ ነው። ተጫዋቾች በሁለት ቡድን ተከፍለው፣ እንደ ባህላዊው ሥርዓት በዱላና በኳስ የሚካሄደውን ጨዋታ ይጫወታሉ። ጨዋታው የአካል ብቃትን፣ ቅልጥፍናንና የቡድን ትብብርን የሚጠይቅ ሲሆን፣ በበዓሉ ወቅት ሰዎች በጋራ የሚደሰቱበት እንቅስቃሴ ነው። የገና ጨዋታ መጫወቻዎች ልዩ ዱላ (ዘንግ) እና ኳስ ነው። ዱላው ስሙ “ገና” ሲባል፣ ከጫፉ ቀለስ ያለ ነው። ብዙ ጊዜ ከወይራ እንጨት ይዘጋጃል። የመጫወቻ ኳስ ስሙ “ሩር” (ጥንግ) ሲባል፣ ከቆዳ ጠፍር ወይም ከጉቶ ተጠርቦ ድቡልቡል ሆና ይሠራል። ጨዋታው በስፋት የሚካሄደው ሰብል በተሰበሰበበት አካባቢ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ በሁለት ቁጥራቸው እኩል በሆኑ ቡድኖች መካከል ሲሆን፣ ተጫዋቾች እግረ ጠባብ ልብስ እና ራሳቸው ላይ ሻሽ አስረው ይጫወታሉ። ጨዋታው ሩሯን በገና ዱላው ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል በማንከባለል እና በመለጋት ነጥብ በማስቆጠር የሚካሄድ ነው። በገና ጨዋታ ብዙ አይነት ውድድሮች የሚከናወኑ ሲሆን ቁርቁዝ፣ ቀልቦ መለጋት፣ አፍሶ መለጋት እና ሙጭ የተሰኙ ውድድሮች ይደረጉበታል። የገና ጨዋታ የሁሉም መሆኑን ለመግለፅ እንዲሁም በጨዋታው ወቅት ለሚፈጠሩ ግጭቶች ቂም መያዝ እንደማይቻል ለማመላከት "በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ" እንዲሁም "በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ" እየተባለ ይዜማል፡፡

የዕለቱን ቀን እና የቀን መቁጠሪያ ዝርዝር በመተግበሪያው ይመልከቱ።

ቀን መቁጠሪያውን በመተግበሪያው ይክፈቱEnglish