ወደ ዋና ይዘት ይሂዱ
ስንክሳር

Appearance

ቀን መቁጠሪያ

ብሔራዊ በዓላት

እንቁጣጣሽ (ዘመን መለወጫ)

ዓመታት ተፈጽመው መስከረም አንድ መጥቶ አዲስ ዓመት ስንጀምር፣ ዕለቱ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ወይም እንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል። መስከረም አንድ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ሲሆን፣ ያለፈውን ዘመን ተሰናብተን አዲሱን ዓመት በተስፋ፣ በምስጋናና በመልካም ምኞት የምንቀበልበት ታላቅ በዓል ነው። እንቁጣጣሽ የአዲስ ዓመት መጠሪያ ብቻ አይደለም። የዝናም ወቅት መገባደድን፣ የምድር መለምለምን፣ የአደይ አበባ መፍካትንና የቤተሰብና የማኅበረሰብ መተሳሰብንም የሚያመለክት በዓል ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ትርጉሙ ጋር ተያይዞ በልዩ ልዩ ባህላዊ ሥርዓቶች፣ በዝማሬና በአበባ ይከበራል።

የእንቁጣጣሽ ስያሜ ትርጉምና አመጣጥ

በከሣቴ ብርሃን ተሰማ የአማረኛ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ መሰረት እንቁጣጣሽ ማለት በክረምት ዘመን በወፈረ መሬት ላይ የሚበቅል እንግጫ ማለት ነው። የእንግጫው ሥር ሽታው ለአፍንጫ የሚጣፍጥ፤ የዐውደ ዐመት ዕለት ልጆች ከአበባው ጋር እያሰሩ ለቤተ ዘመዱ የሚሰጡት፣ ሰጭውም እንቁጣጣሽ ብሎ ሲሰጥ ተቀባዩ በየዓመቱ ያምጣሽ ብሎ የሚመርቅበት ነው። ስለ እንቁጣጣሽ ስያሜ አመጣጥ በሕዝባዊ ትውፊት የሚነገሩ ታሪኮች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ከኖኅና ከልጆቹ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ትውፊት መሠረት፣ ኖኅ ለልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያከፋፍል አፍሪቃ ለካም ደረሰችው። ካምም ወደ አፍሪቃ ሲገባ መጀመሪያ ያረፈበት ምድር ኢትዮጵያ እንደነበረችና በአደይ አበባ እንደሸበረቀች ይነገራል። በዚህ የተደሰተውም «እንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» በማለት ስያሜውን እንዳመጣ ይተረካል። ሌላው ታሪክ ከንግሥተ ሳባና ከንጉሥ ሰሎሞን ጋር ይያያዛል። ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ሰምታ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም በሄደችበት ወቅት ውድ ስጦታዎችን እንዳበረከተችው ይነገራል። በትውፊታዊ ተረኩ መሠረት፣ ሰሎሞንም ለንግሥቲቱ ዕንቁ እንደሰጣትና «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» በማለት እንደመረቃት ይተረካል። ከዚህም በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ እንደመጣ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች አሉ።

ዓውደ ዓመት፣ አራቱ ወንጌላውያንና መጥምቁ ዮሐንስ

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ዓመታት ከአራቱ ወንጌላውያን፣ ከቅዱስ ማቴዎስ፣ ከቅዱስ ማርቆስ፣ ከቅዱስ ሉቃስና ከቅዱስ ዮሐንስ ስሞች ጋር ይያያዛሉ። እነዚህ አራቱ ወንጌላውያን ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ትምህርት፣ ሞትና ትንሣኤ የሚመሰክሩ የወንጌል ጸሐፊዎች ናቸው። ዓመታትን በስማቸው መጥራት በኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር ትውፊት ውስጥ የሚገኝ ልዩ ባህል ነው። ይህ ስያሜ በአራት ዓመት የሚደጋገም ዑደት ውስጥ ይከናወናል። በዚህም የዓመቱ ስያሜ ከወንጌላውያኑ አንዱ ጋር ይያያዛል። በዚሁ የዘመን ስርዓት ውስጥ በየአራት ዓመቱ የምትጨመረው የጷግሜ ተጨማሪ ስድስተኛ ቀን ከዘመነ ሉቃስ ጋር ትያያዛለች። ከዚህ በተጨማሪ መስከረም አንድ በተለየ ከቅዱስ ዮሐንስ ስም ጋር የሚያያዝበት የቤተ ክርስቲያን ትውፊት አለ። ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መካከል እንደ ድልድይ የሚታይ ነቢይ ሲሆን፣ ለጌታችን መንገድ ያዘጋጀ ነው። የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ከእርሱ ስም ጋር መያያዙ የአንድ ዘመን መጠናቀቅንና የሌላ ዘመን መጀመርን በምሳሌያዊ መንገድ ያስታውሳል።

የኢትዮጵያና የግብፅ ቅብጥ ዘመን አቆጣጠር

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከጥንታዊው የእስክንድርያ የዘመን አቆጣጠር ባህል ጋር ታሪካዊ ግንኙነት አለው። በኢትዮጵያ እና በግብፅ የቅብጥ ክርስቲያኖች ዘንድ የሚጠቀሙት የዘመን አቆጣጠሮች በወራት ብዛት፣ በወራት ርዝመትና በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ረገድ ብዙ የሚመሳሰሉ ናቸው። ሁለቱም ዘመን አቆጣጠሮች አሥራ ሦስት ወራት አሏቸው። አሥራ ሁለቱ ወራት እያንዳንዳቸው ሠላሳ ቀናት ሲኖሯቸው፣ የመጨረሻው ወር በኢትዮጵያ ጳጉሜን ተብሎ ይጠራል። ጳጉሜን በመደበኛው ዓመት አምስት ቀናት፣ በዘመነ ዮሐንስ የሚጨመረው ተጨማሪ ቀን ባለበት ዓመት ደግሞ ስድስት ቀናት ይኖሩታል። በሁለቱም የዘመን አቆጣጠሮች አዲስ ዓመት በመስከረም አንድ እና በቅብጥ ወር ቱት መጀመሪያ ይከበራል። በግሪጎሪያን ዘመን አቆጣጠር ይህ ቀን በአብዛኛው መስከረም 11 ላይ ሲውል፣ በተወሰኑ ዓመታት መስከረም 12 ሊውል ይችላል። ስለዚህ መስከረም አንድ የኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት በዓል ብቻ ሳይሆን፣ ከጥንታዊው የእስክንድርያ ክርስቲያናዊ የዘመን ትውፊት ጋር የሚያገናኝ ቀንም ነው።

ባህልና አከባበር

በመስከረም አንድ ማለዳ ቤተሰቦች በአዲስ ልብስ ይዘጋጃሉ። በብዙ ቤቶች የበዓል ምግብ ይዘጋጃል፣ ቡና ይፈላል፣ ዘመድና ጎረቤት ይጎበኛሉ። በዚህ ቀን ልጆች አበባ ይዘው በየቤቱ ይዞራሉ፣ የአዲስ ዓመት ዜማዎችን ይዘምራሉ፣ መልካም ምኞትንም ያካፍላሉ። ለብዙ ክርስቲያኖች በዓሉ በጸሎትና በምስጋና ይጀምራል። ቤተሰቦች ያለፈውን ዓመት በሰላም ስላሳለፉ ያመሰግናሉ፣ ለአዲሱ ዓመትም ጤና፣ ሰላም፣ ፍቅርና በረከት ይለምናሉ። በዓሉ በቤተ ክርስቲያን፣ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ውስጥ የሚታየውን የመተሳሰብ መንፈስ ያጠናክራል።

አደይ አበባ፣ የአዲስ ዓመት ምልክት

አደይ አበባ ከእንቁጣጣሽ ጋር እጅግ የተያያዘ የተፈጥሮ ምልክት ነው። የዝናም ወቅት እየተጠናቀቀ ሲመጣ በሜዳዎች፣ በኮረብታዎችና በመንገዶች ዳር የሚታየው ቢጫ አበባ ምድሪቱን ያሸበርቃል። ይህ የተፈጥሮ ለውጥ የክረምት መገባደድንና የአዲስ ዓመትን መቃረብ ያሳያል። አደይ አበባ አዲስ ጅማሬን፣ ተስፋን፣ የምድርን መለምለምና የሕይወትን መታደስ ይወክላል።

ከቡሄ የሚጀምረው ቅበላ

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ደስታ በመስከረም አንድ ብቻ የሚጀምር አይደለም። ክረምት ወደ መገባደጃው ሲደርስ፣ ዝናም እየቀነሰ ሲመጣና የአዲስ ዓመት ምልክቶች በተፈጥሮ ላይ መታየት ሲጀምሩ፣ በብዙ አካባቢዎች ባህላዊ ዝግጅቶች ይጀምራሉ። ከእነዚህ መካከል ቡሄ (ደብረታቦር)፣ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ሺኖዬና እንግጫ ነቀላ ይጠቀሳሉ። ቡሄ በነሐሴ ወር የሚከበር ሲሆን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን በደብረታቦር ተራራ ላይ መግለጡ ይታሰብበታል። በዚህ ወቅት ልጆች በቡድን በመሆን የቡሄ ዜማዎችን እየዘመሩ በየቤቱ ይዞራሉ። በብዙ አካባቢዎች ችቦ ይያዛል፣ የቡሄ ዳቦ ይዘጋጃል፣ ቤተሰቦችና ጎረቤቶችም በጋራ ያከብራሉ። ልጆች ከሚዘምሯቸው የቡሄ ዜማዎች መካከል፦ «ዶሮ ከጮኸ የለም ለሊት ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት።» የሚለው የሕዝብ አነጋገር ይገኛል። ይህ አነጋገር ቡሄን ከክረምት መገባደድና ከመስከረም መቃረብ ጋር የሚያገናኝ ነው። በዚህ መልኩ የአዲስ ዓመት ደስታ ከበዓሉ ቀን በፊት በልጆች ዜማ፣ በጎረቤት ግንኙነትና በባህላዊ ዝግጅቶች ይጀምራል።

አሸንዳና ሻደይ በሰሜን ኢትዮጵያ

በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በተለይም በትግራይና በአማራ ክልሎች በተለያዩ ስያሜዎች የሚታወቁ የሴቶችና የልጃገረዶች ባህላዊ በዓላት ይከበራሉ። አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ሶለል እና ሌሎች አካባቢያዊ ስያሜዎች ያሏቸው እነዚህ በዓላት ከፍልሰታ ጾም መጠናቀቅ ጋር ተያይዘው ይከበራሉ። በዓላቱ በባህላዊ ልብስ፣ በልዩ የፀጉር አሠራር፣ በሣር ወይም በቅጠል በተሠሩ ጌጦች፣ በልጆች ዝማሬ ይታጀባሉ። ልጃገረዶች በቡድን በመሆን በመንደርና በከተማ ይዞራሉ፣ የተለያዩ ዜማዎችን ይዘምራሉ፣ ይደንሳሉ፣ ዘመድና ጎረቤትንም ይጎበኛሉ። ልጃገረዶቹ በሚይዙት ለምላም ሣር ወይም ወገባቸው ላይ በሚያስሩት ለምለም ቅጠል ክረምቱ እየተገባደደ እንደሆነ ያበስራሉ።

ጎቤ እና ሺኖዬ በሸዋ ኦሮሞዎች ዘንድ

በሸዋ ኦሮሞ ማኅበረሰቦች ዘንድ ጎቤ እና ሺኖዬ በአዲስ ዓመት ወቅት ከሚታዩ ባህላዊ የደስታና የመሰባሰብ ልማዶች መካከል ይጠቀሳል። እንደ አካባቢው ልማድ፣ ልጆችና ወጣቶች በባህላዊ ዜማዎች ይሳተፋሉ። ይህም የአዲስ ዓመትን መቃረብ እና የተፈጥሮን መታደስን የሚያውጅ የአደባባይ ጨዋታ ነው።

እንግጫ ነቀላ በጎጃም

በጎጃም አካባቢ ከአዲስ ዓመት መቃረብ ጋር የሚያያዝ ልዩ ባህላዊ ልማድ እንግጫ ነቀላ ይባላል። በዚህ ልማድ ውስጥ ልጃገረዶችና ሴቶች እንግጫ የተባለውን የዱር ዕፅዋት በመሰብሰብ ከወቅቱ ጋር የተያያዙ ባህላዊ ሥርዓቶችን ያከናውናሉ። ይህ የክረምት መገባደድንና የአዲስ ዓመትን መቃረብ በተፈጥሮ ምልክቶች የሚያሳይ ልማድ ነው።

የዕለቱን ቀን እና የቀን መቁጠሪያ ዝርዝር በመተግበሪያው ይመልከቱ።

ቀን መቁጠሪያውን በመተግበሪያው ይክፈቱEnglish